እረፍት ዐልባ በሆነው ዓለም–ማረፍ

እረፍት ዐልባ በሆነው ዓለም–ማረፍ

ማጠቃለያ

ውጥረትና ዕረፍት የለሽ የሥራ ጫና በርካታ ሰዎችን ያለ ዕድድሜያቸው ወደ መቃብር ያወርዳል፡፡ ነገር ግን በፍጥረት ጊዜ እግዚአብሔር ለውጥረት ችግር ፈውስ አዘጋጅቷል፦ የዕረፍት ቀን! ይህ ቅዱስ ቀን ሰዎች ከሥራቸው አርፈው ከአምላክ ጋር ጊዜ ያሳልፉ ዘንድ በረከት እንዲሆን የታቀደ ነው፡፡ የሚያሳዝነው፣ ምንም እንኳ ሰዎች ዕለቱን ያስታውሱት ዘንድ እግዚአብሔር ሕዝቡን ቢያዝም፣ በርካቶች ይህንን የተለየ ቀን ረስተውታል፤ እንዲያውም ብዙዎች ይህን ቀን የሰጣቸውን ራሱን ፈጣሪ ረስተውታል፡፡

አውርድ

ሚታ ዱራን ሕይወቷ አልፎ ነበር የተገኘችው፡፡ የ24 ዓመቷ ብርቱ የማስታወቂያ ጽሑፍ ባለሙያ፣ በጠረጴዛዋ ላይ ድፍት እንዳለች ነበር የተገኘችው፡፡  ምን አግኝቷት ይሆን?

ሚታ በአንድ የማስታወቂያ ድርጅት ውስጥ ትሠራ የነበረ ሲሆን፣ በድርጅቱ በየዕለቱ የሚጠበቅባት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ የሥራ ጫናው ከባድ ነበር፡፡ ሚታ ከመሞቷ ጥቂት ቀደም ብሎ ምን ያህል በሥራ እንደዛለች የሚጠቁመውን የሚከተለውን መልእክት በማኅበራዊ ሚዲያ አጋርታ ነበር “ያለምንም ማሰለስ ቁልፍ ይዤ ወደ ቢሮ ስሄድ የዛሬው ምሽት ለስምንተኛ ቀን ነው. . . . ሕይወት የለኝም፡፡”

በእስያ የማነቃቃት ባህሪ ባለውና የሬድ ቡል አምሳያ በሆነው በካፊን የበለጸገ፣ ክሬቲንግ ዴንግ የሚባልን መጠጥ በከፍተኛ ደረጃ ትወስድ ነበር፡፡ የመጨረሻው የማህበራዊ ድረ ገፅ የቀጥታ ስርጭት ጽሁፏ “ለ30 ሰዓት በሥራ ላይ ብሆንም ያለድካም ሥራዬን እያከናወንኩ ነው፡፡” የሚል አስተያየት ነበረው፡፡ ከዚያም በቢሮ ጠረጴዛዋ ላይ ድፍት እንዳለች ዳግም ላትነቃ በዚያው አሸለበች፡፡

ምን ተፈጠረ? ሚታ በተደራራቢ የሥራ ጫና ምክንያት ሕይወቷ ሊያልፍ ችሏል፡፡

ዛሬ ብዙዎቻችን የተጨናነቀ የሥራ መርሐ-ግብር አለን፡፡ ማሕበረሰቡ ብዙ እንድንሠራ፣ ብዙ እንድናገኝና ብዙ እድንገዛ ይገፋፋናል፡፡ በጭንቀት፣ በእንቅልፍ እጦት እንዲሁም በአዕምሮ መዛል እንሠቃያለን።

ምናልባት እንደ ሚታ ዱራን ራሳችንን እየገደልን ባይሆንም፣ ነገር ግን ሕይወት በከባድ ሸክም የተሞላ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በፈጣሪ የታቀደልን ይሆን? እርሱ ሰላም ሰጪ ነው። ራሳችንን ከሚገባው በላይ በሥራ ስንወጥር ሰላም ይሰማናል? የለም አይሰማንም!

በድካም የምንዝለፈለፍ ከሆን፣ ፈጣሪ እንድናስታውስ የሚፈልግብንን አንዳች ነገር እየረሳን መሆን አለበት። እስኪ ስለ እርፍት የተናገረው ምን እንደሆነ እንወቅ፡፡

ለአጭር ጊዜ “ዕረፍት” የምናደርግበትን ቁልፍ መጫን፤

ፈጣሪ እጅግ ደግና እጅግ መሐሪ ነው፡፡ ሰብዓዊ ፍጡራን ልክ እንደ ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ወይም ላፕቶፕ ኮምፒዩተር–አካላዊ፣ አእምሮአዊና መንፈሳዊ ኃይላቸውን ለማደስ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ያውቃል። በዚህ የተነሣ ነብዩ ሙሴ (ሙሳ በመባልም ይታወቃል) የፈጣሪን ትዕዛዝ ጻፈ፡-

የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህን ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው። በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ:: (ታውራት ተብሎ ከሚታወቀው ከመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦ ዘጸአት፡ 20፡8–10)።

ይህ የማይለወጥ የእግዚአብሔር ሕግ ሰባተኛውን ቀን እንድናስታውስ ይነግረናል። በዓለም ዙሪያ በሚነገሩ በርካታ ቋንቋዎች፣ ይህ ለእረፍት የተመደበ ሰባተኛ ቀን “ሰንበት” ተብሎ ይጠራል። የሰንበትን ቀን እናስታውስ ዘንድ እግዚአብሔር ለምን አዘዘን? ምክንያቱም መርሳት ከአዳም ጀምሮ እየቀጠለ ያለ የሰው ዘር ችግር መሆኑን ስለሚያውቅ ነው። የፈጣሪን ትእዛዛት መርሳት የለብንም፣ ምክንያቱም በቀናው መንገድ እንደተጠበቅን መመላለስ የምንችለው እርሱን እና ትእዛዛቱን ማስታወስ ስንችል ብቻ ነው።

ነገር ግን ሰንበት የተለየ የሆነው ለምንድን ነው? ፈጣሪ እንዲህ ሲል ይነግረናል፣

ፈጣሪ ሰማይንና ምድርን፤ ባሕርንና በውስጡም ያሉትን ሁሉ በስድስት ቀን ፈጥሮ፤ በሰባተኛው ቀን አርፎአልና፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባረከው፣ ቀደሰውም፡፡ (ዘጸአት፡ 20፡11)::

ሰንበት አምላክ ፈጣሪ እንደሆነ የሚነግረን አስፈላጊ ማስታወሻ ነው። አንዳንዶች ፈጣሪ የማይደክመው አምላክ እንደመሆኑ፣ በሰባተኛው ቀን ማረፍ አያስፈልገውም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ አምላክ ያረፈው ከድካም የተነሳ አይደለም፡፡ ይልቁንም እኛ የምናርፍበትን የተቀደሰ ሰዓት ማበጀት ይችል ዘንድ እነሆ ከፍጥረት ሥራውን አረፈ።

የእረፍት ቀን ለሰው ዘር መልካም እንደሆነ ተመለከተ። ሰባተኛውን ቀን ሰንበት አድርጎ የፈጠረው ሲሆን፣ ይኸውም አረፍ የሚባልበት ወይም ፋታ የሚወሰድበት እንደ ማለት ነው። ስለሆነም የእያንዳንዱ ሳምንት ሰባተኛ ቀን፣ “የእረፍትን” ቁልፍ የምንጫንበት የተለየ ዕለት ነው፡፡ እርሱን ለማስታወስና ለማምለክ ቀኑን ሙሉ ከሥራና ቅዱስ ካልሆኑ እንቅስቃሴዎች ማረፍ ይኖርብናል።

አለቃዎ ወይም መምህርዎ ተጨማሪ እረፍት እንዲወስዱ ቢያዝዎ ግሩም አይደለምን? ፈጣሪ በትክክል ያዘዘው ይህንኑ ነው! ለአምላክ ምስጋና ይግባው! በእርግጥም እርሱ በምሕረት የተሞላ ነው!

የአምላክን ቀን በቅድስና መጠበቅ

ሰንበት በምድር ላሉ ሰዎች ሁሉ ዓለም አቀፋዊ ቅዱስ ቀን ነው። አይሁዶች፣ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች፣ ቡዲስቶች ወይም ሂንዱዎች ከመምጣታቸው አስቀድሞ፣ በእውነተኛው አንድ አምላክ ያምኑ በነበሩ ወገኖች ይጠበቅ ነበር፡፡ ሰንበት ዓለም በተፈጠረበት ወቅት ለመላው ሰብዓዊ ዘር መሰጠቱ እሙን ነው፡፡ አዳምና ሔዋን (ሃዋ በመባልም ትታወቃለች) ሰንበትን ጠብቀዋል፤ እንድናስታውስ የነገረንን እንረሳ ዘንድ አምላክ ፈጽሞ ፈቃድ አልሰጠንም።

በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ሰንበት ብዙ ጊዜ ሲረሳ ይስተዋላል፡፡ የጥንት አይሁዳውያን ሰንበትን የሚረሱ ከሆነ በእግዚአብሔር ጥፋት እንደሚደርስባቸው ነቢያት አስጠንቅቀዋል፡፡ ማስጠንቀቂያውን ሳይሰሙ በመቅረ ታቸው የሩሳሌም ወደመች፣ ቤተሰቦቻቸውም በምርኮ ተወሰዱ። ክርስቲያኖችም እንዲሁ የአምላክን ትዕዛዝ በሚቃረን መልኩ ቅዱስ የሆነውን የአምልኮ ቀናቸውን ወደ እሁድ በመቀየር ሰንበትን እረስተዋል። ሙስሊሞች በአርብ ቀን ይጸልያሉ፣ ለፈጣሪ በፍጹም መታዘዝ ውስጥ መኖር እንችል ዘንድ ሰባተኛውን ቀን መጠበቅ እንዳለብን ግን እረስተዋል።

መላው ዓለም ይህን አስፈላጊ ቀን የረሳ የሚመስለው ለምንድን ነው? ለዚህ ከጫፍ እስከ ጫፍ ለተንሰራፋ የመርሳት ችግር ስውር የክፋት እጅ ይኖርበት ይሆን?

ሰይጣን (ሸይጣን) አእምሯችንን ከፈጣሪያችን ለማራቅ የሚጠቀምበት ዓለም አቀፋዊ ኃይል እንደሚመጣ  መሲሑ የሱስ (ኢሳ አል መሲህ ተብሎም ይጠራል) አስጠንቅቆናል። በሐሰተኛ የሰንበት ቀን አምልኮ ያደርጉ ዘንድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይታለላሉ፡፡ ሰይጣን የፈጣሪንቀን እንድንረሳ ማድረግ ከቻለ፣ ራሱን ፈጣሪን መርሳት የማንችልበት ምክንያት ሊኖር እንደማይችል ያስባል፡፡ ሆኖም እውነተኛውን ሰንበት ስንጠብቅ፣ ለፈጠረን አምላክ ያለንን ታማኝነት በማሳየት በዕለቱ በምናገኘው እረፍትና ሰላም ሐሴት እናደርጋለን፡፡

ወደ አምላክ እረፍት መግባት

ነብዩ ሙሴ “እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባረከው” በማለት ጽፏል (ዘፍጥረት፡ 2:3)፡፡ ደክማችኋል፣ ዝላችኋል? በሰንበት በማረፍ የሚገኙ በረከቶች አሉ!

የማስታወቂያ ጸሐፊዋ ኢንዶኔዥያዊት ሚታ ዱራን ከሥራ ጫና ብዛት ሕይወቷ እንዳለፈ ተመልክተናል፡፡ ይህ ክስተት በእርስዎ ላይ መደገም የለበትም። በሳምንታዊው የሰንበት ቀን ከሥራዎ በማረፍ ፈጣሪ በዕለቱ ያዘጋጀሎትን በረከት ይቋደሱ ዘንድ እነሆ ግብዣውን ያቀርብሎታል፡፡

ፈጣሪ እረፍት፣ ሰላምና ፈውስ እንዴት እንደሚሰጥዎ የበለጠ ማወቅ ከፈለጉ፣ እባክዎ በዚህ ወረቀት ጀርባ ባለው አድራሻ ያግኙን፡፡

Copyright © 2023 by Sharing Hope Publications. ለንግድ ዓላማ አይሁን እንጂ ይህንን ፅሑፍ ማሳተምና ማከፋፈል የተፈቀደ ነው፡፡
በዚህ ጽሁፍ ጥቅም ላይ የዋሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተወሰዱት ከ1993፣ 2003 አዲሱ መደበኛ ትርጉም ነው፡፡

የዜና መጽሔታችንን ለማግኘት ይመዝገቡ

አዳዲስ ሕትመቶች ሲወጡ ለማወቅ የመጀመሪያ ይሁኑ

newsletter-cover