
ታምራት ማየት ይፈልጋሉ?
ማጠቃለያ
ለሕዝቡ በእጅጉ በሚያስፈልጉበት በዚያው ሰዓት እግዚአብሔር በመካከላቸው ታምራትን የማድረግ ረጅም ታሪክ አለው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፍጻሜ ስላገኙ ትንቢቶች፣ ስለ ተፈወሱ ግለሰቦች እና የጸሎት መልስ ሆነው ብቻ ሊከሰቱ ስለሚችሉ አስደናቂ ክስተቶች በርካታ ታሪኮችን ይነግረናል፡፡ ይህ በራሪ ጽሑፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስን የማይለወጥ አምላካዊ ቃል አድርገን ማመን የምንችልባቸውን በርካታ ምክንያቶች ከመስጠቱ በተጨማሪ ለራስዎ ታምራትም እግዚአብሔርን እንዴት መቅረብ እንደሚችሉ ይነግርዎታል፡፡
ዓይነት
Tract
አሳታሚ
Sharing Hope Publications
ይገኛል
48 ቋንቋዎች
ገፆች
6
በርካታ አባላትን ያቀፈ አንድ የቤተሰብ ነገድ፣ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ አንድ አዲስ አገር ለመሰደድ ይወስናል፡፡ ሆኖም ጉዞው ቀላል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ረጅም ርቀት ያለውን ምድረ በዳ በእግራቸው ማቋረጥ ነበረባቸው፡፡ ምድረ በዳው ከሚያስተናግደው ከፍተኛ ሙቀት በተጨማሪ እባቦች እና ጊንጦችም ነበሩበት፡፡ የቤተሰቡ አባላት በሕመም ወይም በድካም ከተጓዦች ተነጥለው ወደ ኋላ ከቀሩ፣ በሽፍቶች ጥቃት ይደርስባቸው ነበር፡፡
ብዙም ሳይቆይ ምግባቸው አለቀ፣ ሆኖም መሪያቸው የፈጣሪን ታምራት ተስፋ በማድረግ ወደ አምላክ ጮኸ፡፡ በሚቀጥለው ቀን ተጓዦቹ ጠኋት ከእንቅልፋቸው እንደ ነቁ፣ ዳቦ የሚመስል አነስተኛ ነገር በመሬቱ ላይ ተበትኖ አገኙ፡፡ በማር እንደተለወሰ ስስ ብስኩት የሚጣፍጥ ነበር፡፡ ከረሀባቸው የሚያጠግብ እና ለሁሉም የሚበቃ አቅርቦት ነበር! ምድረ በዳውን ለማቋረጥ ብዙ ቀናት የወሰደ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ቀን ዳቦ ከሰማይ ይወርድ ነበር፡፡ ለፈጣሪ ምስጋና ይግባውና በመጨረሻ እነዚህ ቤተሰቦች ለመዳን ቻሉ!
ይህ ታሪክ አስገራሚ ሊመስል ቢችልም ሆኖም በእርግጥ የተፈጸመ ነው፡፡ ምናልባት ታውራት፣ ዛቡር እና ኢንጂል በመባል ከሚያውቋቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ከተነገሩ በርካታ ታምራቶች አንዱ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በሕዝቦች ሕይወት ውስጥ በፈጸማቸው በርካታ ታምራቶች ላይ የተመሠረቱ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታሪኮችን ይዟል፡፡ ብዙዎች የራሳቸውን ታምራት በሚሹበት በዚህ ወቅት፣ ለዘመናችን የሚጠቅም መጽሐፍ ነው፡፡
የዚህ ዘመን ታምራቶች
በቅርብ ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነቶችን፣ አብዮቶችን፣ የኢኮኖሚ ውድቀትን፣ ሥራ አጥነትን፣ ተላላፊ በሽታዎችን እንዲሁም ሞትን ተመልክተናል፡፡ በአሁኗ ሰዓት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ከመኖሪያ ቅዬዎ ተፈናቅለው ሊሆን ይችላል፤ አንድ የሚወዱት ሰው በሕይወትና በሞት መካከል እየታገለ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ሥራ ለማግኘት እየታገሉ ይሆናል፡፡
እርስዎ በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ሊገኙ ቢችሉ እንኳ፣ እግዚአብሔር አምላክ ሊጠነቀቅልዎ፣ ጥንት እንዳደረገ ሁሉ ዛሬም ለእርስዎ ታምራት ሊሠራ እነሆ ፈቃደኛ ነው፡፡ ሐዘን ሲሰማዎ የታምራት መጽሐፍ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ ማበረታቻ ማግኘት ይችላሉ፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ለእኛ ዘመን
አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በተወሰነ መልኩ ተቀይሮአል የሚል ወሬ መስማታቸውን ተከትሎ ለማንበብ ዳተኞች ሲሆኑ ይስተዋላሉ፡፡ ምናልባት ለዚህ የተሳሳተ አመለካከት መንስዔው መጽሐፍ ቅዱስን እንከተላለን የሚሉ በርካታ ሰዎች ከሚከተሉት የኑሮ ዘይቤ አኳያ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች አስካሪ መጠጥ ሲጠጡ፣ ቁማር ሲጫውቱ፣ አግባብ ያልሆነ ልብስ ሲለብሱ፣ የዐሣማ ሥጋ ሲበሉ እንዲሁም ሰዎችን በጎነት በጎደለው አኳኋን ሲያስተናግዱ እንመለከታለን፡፡
ሆኖም እነዚህ ስህተቶች በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ የተወገዙ ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ መኖራቸው፣ ዘላለማዊ የሆነውን የቃሉን ትክክለኛነት አይለውጠውም፡፡ ነብዩ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ጽፎአል፡ “ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፣ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፡፡” (ኢሳይያስ፡ 40፡8)፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ይለውጡ ዘንድ የሰው ልጆች በቂ ጉልበት ያላቸው ይመስሎታል ወይስ እንዲያው በመጥፎ ባህሪ ያለ አግባብ እየወከሉት ነው?
ነብዩ ዳዊት (ዳውድ በመባልም ይታወቃል) እና ህዝቡ የቃል ኪዳኑን ታቦት ማለትም አስርቱን ትእዛዛት የያዘውን የወርቅ ሳጥን ሲያጓጉዙ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ለግብረገባዊ የአኗኗር ዘይቤ አስፈላጊ የሆኑት አምላካዊ ሕግጋት ማለትም አሥርቱ ትዕዛዛት በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ተጽፈው ከወርቅ በተሠራው ታቦት ውስጥ ተቀምጠው ነበር፡፡ በጉዞው ላይ አንድ ሰው እጁን ሰዶ ታቦቱን ለመንካት ደፈረ—ወዲያውም ወድቆ ሞተ!
እብሪተኛ እጆች ቃሉን የያዘውን ቅዱሱን የምስክሩን ታቦት ይነኩ ዘንድ የማይፈቅድ ከሆነ፣ ርኩስ ሰዎች መቀስና እርሳስ ይዘው ለእርማት ወደ ቅዱስ ቃሉ ይቀርቡ ዘንድ ምን ያል ሊፈቅድ ይችላል? ፈጣሪ ቃሉን የተጠበቀ ያደርግ ዘንድ ታላቅ ኃይል ያለው አምላክ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ልጆች ታሪክ እጅግ ተረጋግጦ የቀረበ መጽሐፍ ስለመሆኑ በተጨባጭ መናገር እንችላለን፡፡ ቤዶዩን በመባል ከሚታወቅ አርብቶ አደር የአረብ ጎሳ አባላት የሆኑት የፍልስጥኤም እረኞች፣ መሐመድ ኢዳ-ዳሂብ፣ ጁምአ መሐመድ እና ካሊል ሙሳ–በድንገት ጥንታዊዎቹን የሙት ባሕር ጥቅል ጽሑፎች ያገኙት በቅርቡ ነበር፡፡ ይህ ክስተት የዛሬውን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ 2,000 ዓመታት ገደማ ዕድሜ ካላቸው ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ጽሑፎች ጋር እንድናወዳድር ያስቻለን ታላቅ የአርኪዮሎጂ ግኝት ነበር፡፡ ይህ የእጅ ጽሑፍ ቅጂ አሁን በእጃችን ካለው መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያለው ተመሳሳይነት አስደናቂ መሆኑ፣ አምላክ የሚሰጠው መገለጥ ሊለወጥ የማይችል መሆኑን በድጋሚ ያመላከተ ነው፡፡ ታምራት ማየት የሚፈልጉ ከሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሊያነቡት የሚገባ ተአማኒ መልእክት ለመያዙ እርግጠኛ መሆን ይችላሉ! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ኖኅ (ኑህ)፣ አብርሃም (ኢብራሒም)፣ ዮሴፍ (ዩሱፍ)፣ ዮናስ (ዩኑስ)፣ ዳንኤል፣ ዳዊት (ዳውድ)፣ እና ሰለሞን (ሱለይማን) የመሳሰሉትን ነቢያት ግሩም ታሪኮች ያገኛሉ፡፡ ስለነዚህ ነቢያት ከሌላ ስፍራ ያልተሟሉ ታሪኮችን ሰምተው ይሆናል፡፡ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ታሪካቸውን ይናገራል፡፡
ይምጡና በእርስዎ ላይ ታምራት ሲሆን ይመልከቱ!
በየትኛውም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ እንኳ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለእርስዎ የሚሆን የታምራት ታሪክ አለው፡፡
እርስዎ ወይም የሚወዱት የቤተሰብ አባል ህመም ገጥሞት ይሆን? ለምጽ ወጥቶበት የነበረው ንዕማን የተባለው የሶርያ ንጉሥ ጦር አዛዥ በታምር የመፈወሱን ታሪክ ያንብቡ፡፡
ቤተሰብዎን መመገብ ፈታኝ ሆኖቦት ይሆን? በትንሽ ማሰሮ ውስጥ የነበረ ዘይትና በማድጋ የነበረው ጥቂት እፍኝ ዱቄት ሳያልቅባቸው ረዥሙን የረሃብ ዘመን ስላሳለፉት ሊባኖሳዊት መበለትና ወንድ ልጇ ያንብቡ፡፡
ሕይወትዎ በአደጋ ውስጥ ነው? እግዚአብሔር ላይ በነበረው እምነት በጦርነት ጊዜ ሕይወቱ ስለተረፈችለት በንጉሡ ቤተ መንግሥት ውስጥ ስለ ነበረው ኢትዮጵያዊ ባሪያ አቤሜሌክ ያንብቡ፡፡
በሌሎች የተጠሉ ወይም የተገለሉ ሆኖ ይሰማዎታል? ነቀፋ በደረሰባት ወቅት አምላካዊ ተምራት ስላየችው ግብጻዊቷ አጋር ታሪክ ያንብቡ፡፡
በውጥንቅጥ በተሞሉ የሕይወት ችግሮች እየሰጠሙ ሆኖ ይሰማዎታል? ደቀ መዛሙርቱን ከጀልባ የመስጠም አደጋ ለመታደግ እጁን ዘርግቶ ኃይለኛውን ሞገድ ጸጥ ስላደረገው የሱስ ክርስቶስ ያንብቡ፡፡
ታምራዊ መልሶች
መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ አዎንታዊ ምላሽ ጠብቀን እንድንጸልይ በሚያደርግ መተማመን እንሞላለን፡፡ የሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ተናግሮአል፡ “እምነት ካላችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ፡፡” (ማቴዎስ፡ 21፡22)፡፡ ከጌታ ታምራት የተቀበሉ ሰዎችን ታሪክ ስናነብ፣ እኛም ልመናዎቻችንን ወደ ሰማይ ለማቅረብ ልባችን በተስፋ ይበረታታል፡፡
ታምራት ማየት ይፈልጋሉ? መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባሉት ታምራቶች እየተበረታቱ ፈጣሪ በእርስዎም ላይ ታምራቱን ያደርግ ዘንድ ይጠይቁት፡፡ እርሱ ጸሎትዎን በእርግጠኝነት ዛሬውኑ ይሰማል!
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለቀረቡ ታምራቶች ይበልጥ ማወቅ የሚፈልጉ ከሆነ፣ እባክዎ በዚህ ወረቀት ጀርባ ባለው አድራሻ ይጻፉልን፡፡
Copyright © 2023 by Sharing Hope Publications. ለንግድ ዓላማ አይሁን እንጂ ይህንን ፅሑፍ ማሳተምና ማከፋፈል የተፈቀደ ነው፡፡በዚህ ጽሁፍ ጥቅም ላይ የዋሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተወሰዱት ከ1993፣ 2003 አዲሱ መደበኛ ትርጉም ነው፡፡
የዜና መጽሔታችንን ለማግኘት ይመዝገቡ
አዳዲስ ሕትመቶች ሲወጡ ለማወቅ የመጀመሪያ ይሁኑ
