ስለ ራስዎ እንዴት ማሰብ እንዳለብዎ፤

ስለ ራስዎ እንዴት ማሰብ እንዳለብዎ፤

ማጠቃለያ

የእግዚአብሔር ነቢያት “ባቢሎን” በሚል ምሳሌ ስለተገለጸው አደገኛ ኃይማኖታዊ ኃይል ተንብየዋል፡፡ በትንቢቱ መሠረት፣ ይህ ኃይል ሐሰተኛ አምልኮ ውስጥ እንድንገባ ሊያስገድደንና ሊያባብለን ይሞክራል፡፡ ደኅንነትን ማግኘት የምንችልበት ብቸኛው መንገድ፣ ስለ ራሳችን በማሰብ እና ለተገለጠው አምላካዊ ቃል ጥብቅ ታማኝነት በማሳየት ብቻ ነው፡፡ በዓለማቀፋዊ ቀውስ ወቅት ልባሞችና ጥበበኛ አማኞች ሆነን ለመገኘት አእምሮአችንን እንዴት ማሠራት እንዳለብን ይህ በራሪ ጽሑፍ ይነግረናል፡፡

ዓይነት

Tract

አሳታሚ

Sharing Hope Publications

ይገኛል

48 ቋንቋዎች

ገፆች

6

አውርድ

ከረጅሙ አቀበታማ የእግር ጉዞ በኋላ ጉኑንግ ዳቱክ በመባል የሚታወቀው ተራራ ጫፍ ላይ ደረስን፡፡ ከፊቴ የተንጣለለውን አድማስ በዐይኖቼ እያማተርኩ ለማጣጣም ከአዲሱ ጓደኛዬ አድዘክ አጠገብ አረፍ አልኩ፡፡ ብዙም ሳይቆይ፣ ውይይታችን ወደ ኃይማኖታዊ ርዕሰ ጉዳይ ዞረ።

“ነፃ አስተሳሰብ አራማጅ ነኝ” አለ አድዘክ፡፡ “ስለ ዓለም የራሴ የሆነ ዕይታ አለኝ፡፡”

“አሃ፣ እሺ” አልኩኝ፡፡ “በርካታ የማሌዥያ ወጣቶች ራሳቸውን እንደ ነፃ አስተሳሰብ አራማጅ እንደሚያዩ ሰምቻለሁ።” ስለው፣

አድዘክ ሣቀ፡፡ “ስለ ራሳችን ማሰብ አለብን፤ ያለበለዚያ በርካታ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች ከመኖራቸው አኳያ፣ ሊያሳብዱህ ይችላሉ::”

“ወደ ቤት ስትሄድስ ተመሳሳይ አቋም ነው የምታራምደው?” ስል ጠየቅኩት፡፡ “እዚህ ማሌዥያ ውስጥ በርካታ ወጣቶች ራሳቸውን የነፃ አስተሳሰብ አራማጅ አድርገው ይመለከታሉ፣ በቤት ውስጥ ግን በእስልምና ወይም በቡድሃ ኃይማኖታዊ ሥርዓቶች እንድትሳተፍ ይጠበቅብሃል፡፡ ለወላጆችህ ምን ትላቸዋለህ?” ብዬ ለጠየቅኩት ጥያቄ፣

“ምንም አልላቸውም” ሲል መለሰ ልኝ፡፡ ነፃ አስተሳሰብ ማራመድ ብችልም፣ ነገር ግን ጉዳዩን ለራሴው በምስጢር መያዝ ይኖርብኛል፡፡

ነፃ አስተሳሰብ ማራመድ አስፈላጊ ነው?

በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች በብዙዎች ከተለመደው ያፈነገጠ እምነት ማራመድ፣ ከማሕበረሰቡ ሊያስገልል፣ ከሥራ ሊያስባርር ወይም ከነጭራሹ ሊያስገድል ይችላል፡፡ የግል አስተሳሰብ ማራመድ አደገኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይህ ሁሉ አስፈላጊ ነው?

ዓለማችን በበጎ እና ክፉ አስተሳሰቦች የተሞላች ናት፡፡ በጎውን ነገር ክፉ ከሆነው ለመለየት የሚያስችል ምርመራ ለመጀመር፣ በቅድሚያ ስለ ጉዳዩ ማሰብ እና መነጋገር አንዱ ጠቃሚው አካሄድ ነው፡፡ እንደ ወርቅ፣ ሳፍሮን ወይም አይፎን ያለ ውድ ነገር ለመግዛት ፈልገው ከሆነ፣ እንደማንኛውም ተራ ነገር ብድግ አድርገው ከፍለው አይሄዱም፡፡ ይልቁንም የተሻለው ሥሪት እጅዎ ለመግባቱ እርግጠኛ ይሆኑ ዘንድ ጥራቱን ይፈትሻሉ፣ ምርቱንም ከሌሎች ሻጮች አኳያ ያነጻጽራሉ፡፡ በተመሳሳይ ሀሳቦችም በነፃነት ሊንሸራሸሩ ይገባል፡፡

በዓለም ብዙ ግራ መጋባት አለ፤ ሰዎች የራሳቸውን ግራ የተጋቡ ሐሳቦች በማሕበረሰቡ ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ደግሞ ነገሩ ይባባሳል። አንድ በእጅጉ ጠቃሚ ስለሆነ ትንቢታዊ መልእክት ልንገርዎ፡፡ “የየሱስ ክርስቶስ ራእይ” በመባል የሚታወቅ አንድ በጣም ጥንታዊ መጽሐፍ፣ የራሳቸውን ግራ የተጋቡ ኃይማኖታዊ አመለካከቶች በሌሎች ላይ ለመጫን ስለሚሞክሩ ሕዝቦች በትንቢት ይነግረናል፡፡ “ሕዝቦች ሁሉ የዝሙቷን ቁጣ ወይን ጠጅ እንዲጠጡ ያደረገች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች!”  (ራእይ 14፡8) ይላል፡፡

እነዚህ ምሳሌያዊ ቃላት ለማስተዋል የሚከብዱ አይደሉም። ባቢሎን ዝነኛ ጥንታዊ ከተማ የነበረች ሲሆን ስሟ “ድንግርግር” የሚል ፍቺ አለው፡፡ ከተማዋ “ወደቀች” የተባለችው ግራ ስለተጋባች ሳይሆን፣ ግራ መጋባትዋን መተው ስለማትፈልግ ነው፡፡ መንፈሳዊ ዝሙትዋን እንዲቀላቅሉ ሕዝቦችን የምታባብል ሲሆን፣ ይኸውም እውነተኛና ሐሰተኛ አምልኮን በማቀላቀል በፈጣሪ ላይ ክህደት መፈጸም ነው፡፡ እነዚህ ሐሰተኛ እሳቤዎች የተለመዱና ተቀባይነት ያላቸው ተደርገዋል፡፡ ስለ “ባቢሎን” የተነገረው ትንቢት ዓለማቀፋዊ መንፈሳዊ ተቋምን ያመለክታል፡፡ ይህ ተቋም መንፈሳዊ ዕፀፆችን እንደ ትክክል በመፈረጅ ብቻ ሳይገታ፣ ውሎ አድሮ በእውነት ላይ የተጣበቁ ሰዎች ላይም ይህን ስህተት በግድ ለመጫን የሚሞክር ዓለማቀፋዊ ኃይማኖታዊ አካል ነው፡፡

ይህ በእኛ ዘመን እውን እንደሚሆን የየሱስ ክርስቶስ ራእይ ተንብዮአል። ምናልባት የክስተቱን ገቢራዊ መሆን ከወዲሁ ተመልክተው ሊሆን ይችላል፡፡ በሐሰተኛ አስተምህሮ ፈጣሪን የሚወክሉ ሕዝቦች ይኖሩ ይሆን? የሕሊና ምቾት የማጣት ስሜት ተሰምቶት ያውቃል?

አዎ፣ ነፃ አስተሳሰብ አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው፡፡

ስለ ገዛ ራስዎ ሊኖርዎ የሚገባ አስተሳሰብ፤

በርካታ ሰዎች የማሕበረሰባቸውን ኃይማኖት በመከተላቸው ደስተኞች ናቸው፡፡ እምነታቸውን አይመረምሩትም፡፡ ምንም ትርጉም የማይሰጡ ወይም ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው የሚያመዝኑ ኃይማኖታዊ ልምዶችን ይከተላሉ፡፡ ወደ አምላክ የሚወስደውን መንገድ ሊያሳዩን የሚገባቸው ራሳቸው የኃይማኖት መሪዎች ሳይቀሩ አንዳንዴ በአጓጉል ድርጊቶች ተዘፍቀው ይስተዋላሉ፡፡

እውነትን ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በነቢያት ላይ መተማመን ይኖርብናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምን? ለዚህ ሦስት ምክንያቶች አሉ፡-

  1. ነቢያት ስለወደፊቱ አስደናቂ እውቀት እንዳላቸው ያሳያሉ፡፡ አውሮፓ ዓለምን ቅኝ ወደምትገዛበት ታሪካዊ ደረጃዋ እንደምታድግ ነብዩ ዳንኤል ተንብዮአል። የሱስ ክርስቶስ (ኢሳ አል-መሲህ በመባልም ይታወቃል) በ70 ዓ.ም. ላይ ገቢራዊ የሚሆነውን የየሩሳሌም ውድመት አስቀድሞ ተንብዮ ነበር፡፡ ነብዩ ሙሴ (ሙሳ) እስከ ዘመን መጨረሻ ያለውን የእስማኤል ታሪክ ተንብዮአል፡፡

  2. ነቢያት ስለ ጤና አስገራሚ ሳይንሳዊ ዕውቀት እንዳላቸው በጉልህ ይታያል፡፡ ከ3,500 ዓመት በፊት አካባቢ የኖረው ነብዩ ሙሴ በተላላፊ በሽታ የተያዘን ሰው ለብቻ ለይቶ ስለ ማቆየት፣ ለመጸዳጃ የሚሆን ስፍራ ስለ ማዘጋጀት እንዲሁም መጠቀሚያ ቁሶችን ከበሽታ አስተላላፊ ተህዋስያን ነጻ ስለ ማድረግ አብራርቶአል፡፡ እንስሳትን ንጹህ እና ንጹህ ያልሆኑ ብሎ ከፍሎአል፡፡ ንጹህ በሚል ከተመደበው ሥጋ በምንመገብበት ጊዜ ደም ወይም ስብ እንዳንበላ ነግሮናል፡፡ ዛሬም ቢሆን እርሱ ያዘዘውን የአመጋገብ እና የንጽህና ሕግ የሚከተሉ ሁሉ አጠቃላዩ ሕዝብ ከሚኖረው ዕድሜ ተጨማሪ 15 ዓመት ይኖራሉ፡፡

  3. ፈጣሪ በእርሱ የሚታመኑትን እና ነቢያቱን የሚቀበሉ አማኞችን ጸሎት ይመልሳል፡፡

የነቢያቱ ጽሁፎች በምሪት የተሞሉ ናቸው—ነገር ግን ከእነርሱ ጥቅም ለማግኘት፣ በአንክሮ ማሰብን፣ እምነቶቻችንን መፈተንና በእምነታችን ዙሪያ ያለውን ማስረጃ መፈተሽን መማር የግድ ያስፈልገናል፡፡ በአንክሮ ማሰብ የእውነተኛ ኃይማኖት አስፈላጊ አካል ነው፡፡

የስህተት አስተምህሮን ስንመረምር ምን ይፈጠራል? ላይ ላዩን ሲያዩት እውነት ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን መረጃ ስንፈልግ፣ በሐሳቡ ላይ ችግር መኖሩን ማየት እንጀምራለን፡፡

እውነት ደግሞ ልክ የዚህ ተቃራኒው ነው፡፡ እውነት በጥንቃቄ ሲመረመር አንዳች የሚጎድልበት ነገር አይኖርም፡፡ አብልጠን ምርመራ ባደረግን ቁጥር እውነት ከቀድሞው ይበልጥ እየፈካና እየደመቀ ይመጣል፡፡

እግዚአብሔር በጥበብ ጎዳና ስለሚመራን፣ አማኞች የዓለማችን ተወዳዳሪ የሌላቸው ጠቢባን መሆን ይገባቸዋል፡፡ ጥያቄ ለመጠየቅ ወይም በነፃነት ለማሰብ በማይፈቀድላችሁ ሁኔታ ውስጥ ራሳችሁን የምታገኙ ከሆነ፣ ይህ ከአምላክ ዘንድ አይደለም፡፡ እውነት በሚደረግበት ምርመራ ፊት ለመቆም ያለው ጥንካሬ ከብርቱ በላይ በመሆኑ ቀረብ ብለን እንመረምረው ዘንድ ይጋብዘናል፡፡ ነገር ግን ባቢሎን ወደ ሐሰት በመገፋፋትና አእምሮ ለመመርመር የሚያደርገውን የጥረት በር በመዝጋት ባሉበት ይቀሩ ዘንድ ታግባባዎታለች፡፡

በባቢሎን ውስጥ ያሉ ዓይነት ግራ መጋባት የሚሰማዎ ከሆነ፣ እነሆ ከእርሷ ይውጡ! ወደ አምላካዊው የጥበብ ጎዳና ይምጡ፡፡ ስለ ገዛ ራስዎ በማሰብ ጥብቅ ጥያቄዎችን ይጠይቁ፡፡ ቅር የሚሰኙበት ነገር አይገጥሞትም፡፡

ስለ የሱስ ክርስቶስ ራእይ የበለጠ ማወቅ ይፈልጋሉ? እባክዎ በዚህ ወረቀት ጀርባ ባለው አድራሻ ያግኙን፡፡

Copyright © 2023 by Sharing Hope Publications. ለንግድ ዓላማ አይሁን እንጂ ይህንን ፅሑፍ ማሳተምና ማከፋፈል የተፈቀደ ነው፡፡
በዚህ ጽሁፍ ጥቅም ላይ የዋሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተወሰዱት ከ1993፣ 2003 አዲሱ መደበኛ ትርጉም ነው፡፡

የዜና መጽሔታችንን ለማግኘት ይመዝገቡ

አዳዲስ ሕትመቶች ሲወጡ ለማወቅ የመጀመሪያ ይሁኑ

newsletter-cover