
ምሕረትን መናፈቅ
ማጠቃለያ
ለመሆኑ አምላካዊው ምህረት ምን ይመስላል? እንዲሁ “ይቅር ብዬሃለሁ” ብቻ ይለናል ወይስ አሳፋሪውን መዝገባችንን የሚያነጻ ምትክ ያቀርብልናል? የየሱስን ለሰብዓዊው ዘር ምትክ መሥዋዕት የመሆን አስፈላጊነትና ፍቺ በሚገባ መግለጽ ይቻል ዘንድ፣ ይህ በራሪ ጽሑፍ በአገር በቀል ታሪክ ላይ የተመረኮዘ መልእክት ያካፍላል፡፡ አንባብያን ኃጢአታቸው ይቅር ሊባል እንደሚችልና ሐፍረታቸውም እንደሚወገድ ማወቃቸው ተስፋ እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል፡፡
ዓይነት
Tract
አሳታሚ
Sharing Hope Publications
ይገኛል
48 ቋንቋዎች
ገፆች
6
ፋጢማ ዓመታዊውን የኢድ አል አድሃ በዓል ብቻዋን ለማሳለፍ በመገደዷ እየተሰማት ያለውን የብቸኝነት ስሜት መቋቋም አቅቷታል፡፡ ለነገሩ በዓሉን በብቸኝነት እንድታሳልፍ ጥፋቱ የራሷ እንጂ ሌላ የማን ሊሆን ይችላል?
ፋጢማ፣ አህመድን በማግባቷ ከአባቷ ጋር እንዴት እንደተካረሩ ትውስ አላት፡፡ በወቅቱ ገና አፍላ ወጣት የነበረችው ፋጢማ፣ በመሐመድ ፍቅር ወድቃለች፡፡ ታዲያ አባቷ ለዚህ ግንኙነት እንዴት ይሁንታቸውን መንፈግ ተቻላቸው? ፋጢማ መሐመድን ብላ ከቤት ኮብልላ ስትወጣ፣ ከዚህ በኋላ ቤት አለኝ ብላ እንዳትመለስ አባቷ አስጠንቅቀዋት የነበረ ቢሆንም፣ ለአህመድ ካላት ፍቅር የተነሳ የሚመጣውን ሐፍረት መቋቋም የምትችል መስሎአት ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ አባቷ ትክክል እንደ ነበሩ ለማመን ተገደደች፡፡
አህመድ፣ እርስዋ እንዳሰበችው በፍቅር የወደቀችለት ወንድ ሆኖ አላገኘችውም ፤ እርሷን ትቶ ወደ ሌላዋ ሄዷልና፡፡
በገዛ ራሷ ውሳኔ የተጸጸተችው ፋጢማ፣ እንግዲህ የእጄን ነው ያገኘሁት፣ ይበለኝ አለች፡፡ ሰው የእጁን ማግኘቱ ምን ማለት እንደሆነ አሁን በሚገባ ተረድታለች፡፡ ሆኖም ልቧ ይቅር መባልን ምንኛ ናፍቋል!
ፈጣሪ እጅግ ደግ እና በምሕረት የተሞላ አምላክ ነው፤
እውነት እንነጋገር ከተባለ ሁላችንም ስህተቶችን ሠርተናል፤ የጥበብንም ድምፅ ቸል ብለናል። ሌሎችን አሳዝነናል። ሌሎችም አሳዝነውናል። የማኅበረሰባችን አካል የሆኑት ሰብዓዊ ፍጡሮች ስህተት የሚሠሩ ሰዎች አካል ናቸው፡፡ እርስ በርሳችን ብሎም የገዛ ራሳችንን ይቅር ማለት ምንኛ ከባድ ነው?
ለስህተቶቻችን ይቅርታ ማግኘት ይቻል ይሆን?
“ቢስሚላህ አል-ራህማን አል-ራሂም”—“እጅግ በጣም ርኅሩኅ፣ በጣም አዛኝ በሆነው በፈጣሪ ስም” የሚለውን ቀለል ያለ ሐረግ ስንት ጊዜ እንደደጋገሙት አሰብ ያድርጉ፡፡ ለመሆኑ ይቅር መባልን ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?
ምናልባት ማኅበረሰባችን ብሎም የገዛ ልባችን አብልጦ ይቅር መባል ስለሚያሻው ሊሆን ይችላል፡፡
ምሕረት ማድረግ፡ የተሻለው መንገድ
ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ አብዱል ራህማን የተባለ ሰው ጎረቤቱ ከነበረው ካሪም ጋር ተደባደበና ሕይወቱ እጁ ላይ አለፈ፡፡ ይህ አሳዛኝ ክስተት በተፈጸመባት በዚህች አነስተኛ የግብፅ መንደር፣ ሕይወት ለሟችም ሆነ ለገዳይ ቤተሰቦች ባለችበት የቆመች መሰለች፡፡ የካሪም ቤተሰቦች ለበቀል ሲነሣሱ፣ የአብዱል ራህማን ቤተሰቦች ደግሞ በፍርሐት ከበቀል ጥቃት ሊታደጉት ሞከሩ፡፡ አብዱል-ራህማን የበቀል አዙሪቱ እንዲቀጥል አልፈለገም። የመንደሩን ሽማግሌዎች ሲያማክር፣ በከፈን ጨርቅ የመገነዝ ሥርዓት እንዲያካሂድ ምክረ ሀሳብ ሰጡት፡፡
አብዱል ራህማን ራሱ የሚገነዝበትን ነጭ የከፈን ጨርቅ አመጣና በላዩ ቢለዋ አስቀመጠ፡፡ ግልብጥ ብሎ የወጣው መላው የመንደሩ ሰው እያየው፣ የካሪምን ቤተሰብ ለመገናኘት ወደ ገበያው ስፍራ አመራ፡፡ አብዱል ራህማን የሟች ወንድም በሆነው ሀቢብ ፊት ተንበረከከና የከፈኑን ጨርቅ እና ቢለዋ በመስጠት፤ ምኅረት እና እርቅ በመሀላቸው ይወርድ ዘንድ ጠየቀ፡፡
ሀቢብ ቢላውን በአብዱል ራህማን እንገት ላይ አሳረፈ፡፡ የመንደሩ ሽማግሌዎች የበግ ጠቦት አመጡ፡፡ እናም ሀቢብ መወሰን ነበረበት–ምሕረት ወይስ በቀል? ቢላውን በአብዱል-ራህማን አንገት ላይ ሲያሳርፍ ሳለ፣ ድርጊቱ፡ “አሁን በቁጥጥሬ ሥር ነህ፣ ደግሞም፣ የሁሉም ዐይኖች ይህን ክስተት እያዩ ናቸው፡፡ እገድልህ ዘንድ መብቱም ሆነ ችሎታው እንዳለኝ ሁሉም ያውቃል፡፡ ነገር ግን ምሕረትንና እርቅን መርጫለሁ። ደም የመቃባት አዙሪት በእዚህ እንዲቋጭ አድርጌአለሁ፡፡” ብሎ ያወጀ ይመስል ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ እጁን ከአብዱል ራህማን ላይ አነሣና በምትኩ የበጉን ጠቦት አረደው፡፡ በሀቢብ ውስጥ የነበረው ህመም፣ ቁጣ እና የፍትሕ ጥማት በእንስሳው ደም ሲከስም፣ ሀቢብ በአብዱል ራህማን ላይ ተጠመጠመ፡፡ በሁለቱ ቤተሰቦች መካከል ሰላም ወረደ።
ሰብዓዊ ፍጡራን ይቅር በማለት ፍትሕ ማስፈን እስከቻሉ ድረስ ፈጣሪም በእርግጠኝነት ይህንኑ ማድረግ ይችላል፡፡
መሲሑ የሱስ፡ ምሕረት ከፈጣሪ ዘንድ
ስለ ፈጣሪ ምሕረት ከወዴት መማር እንችላለን? ይህን ለማወቅ ብዙም ከባድ አይደለም፡፡ መሲሑ የሱስ (ኢሳ አል-መሲሕ በመባልም ይታወቃል) “ምሕረት” ከፈጣሪ ዘንድ ተብሎ እንደሚጠራ ሳይሰሙ አይቀሩም፡፡ ይህ ደግሞ እርሱ ፍጹም በሆነ መንገድ ምኅረትን ይወክላል ማለት ነው፡፡ የእርሱ መንገድ—ኢንጂል በመባልም በሚታወቁት በወንጌላቱ ውስጥ ያሉት ትምህርቶቹ—የይቅርታና የእርቅ ጎዳና ነው፡፡
መሲሑ የሱስ እንደዚህ ዓይነት ግሩም ሚና መጫዎት ይችላል፣ ምክንያቱም ብቸኛው ከኃጢአት ፍጹም ነፃ የሆነ፣ ከፈጣሪ የተላከ እርሱ ነው። እያንዳንዱ ነቢይና ቅዱስ መልዕክተኛ ስለጥፋታቸው ይቅርታ ያስፈልጋቸው ነበር፤ ለመሲሑ የሱስ ግን አላስፈለገውም። እስከ ፍርድ ቀን ከመጠበቅ ይልቅ በቀጥታ ወደ ሰማይ ተወሰደ፤ እርሱ ቅንጣት ያህል እንኳ ስህተት አልሠራምና፡፡
በዚህም ምክንያት እርሱ ምሕረት ከፈጣሪ ዘንድ ተብሎ ተጠራ። ንጹህ ስለሆነው ምሕረት ምሳሌ በመተው አምላካዊውን ይቅርታ እንዴት መቀበል እንደሚቻል አስተማረ፡፡
መሲሑ የሱስ እንዴት ሊረዳኝ ይችላል?
መጥምቁ ዮሐንስ (ያህያ በመባልም ይታወቃል) የሱስን በሕዝብ መካከል እንዳየው፣ በፈጣሪ መንፈስ ሥር ሆኖ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ!” (ዮሐንስ ወንጌል፡ 1፡29) ብሎ እንደጮኸ ተጽፏል፡፡ መሲሑ የሱስ ለአብዱል-ራህማን የእርቅ መንገድ እንደ ከፈተለት በግ ነው ማለት ነው።
ስለ ጥፋቶቻችን ከተቀጣን፣ ይህ ፍትሕ ነው። ሆኖም ፍጹም ኃጢአት ዐልባ የሆነው መሲሑ የሱስ ለስህተቶቻችን ኃላፊነቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ ሆነ። ይህን ያደርግ ዘንድ ማንም አላስገደደውም፡፡ የፍትሕን ጥያቄ ይመልስ ዘንድ ራሱን በፈቃደኝነት መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፡፡ እርሱ ፍጹም ከበደል ነጻ ሕይወት የኖረ ብቸኛ ሰው ቢሆንም፣ ነገር ግን በአብዱል-ራህማን ታሪክ ውስጥ እንደተጠቀሰው የበግ ጠቦት ፍትሕ የሚጠይቀውን ቅጣት በመቀበል ይስተናገድ ዘንድ ፈቀደ፡፡ ለእኛ ከተሰቃየ በኋላ ፈጣሪ አስነስቶት ወደ ሰማይ የወሰደው ለዚህ ነው።
ምናልባት በሕይወትዎ ጥል እና አለመግባባት ገጥሞት ይሆናል፡፡ ምናልባትም እንደ ፋጢማ በሚወዱት የቤተሰብ አባል ከቤት የመባረር ዕጣ ደርሶቦት ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባት በሆነ ሰው ተጎድተው ወይም ክብርና ዝናዎ ያለ አግባብ ጎድፎ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባት እርስዎም እንደ አብዱል ራህማን ጥፋተኛ እና በበቀል ፍራቻ ውስጥ የሚገኙ ሰው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ሆኖም መሲሁ የሱስ ሊረዳዎ ይችላል፡፡ እንደሚከተለው ያለ አጭር የልመና ቃል ማቅረብ ይችላሉ፡
አቤቱ ጌታ ሆይ ለበደሌ ካሳ የሚሆን አንዳችም ነገር ማቅረብ አልችልም፡፡ ነገር ግን መሲሁ የሱስን የአንተ ምሕረት አድርገህ ወደ እኛ እንደላከው አውቃለሁ፡፡ እርሱ ስለ መላው የሰው ዘር ለሠራው መልካም ሥራ ስትል አቤቱ ይቅር በለኝ፡፡ ምሕረትሕን በሕይዎቴ መለማመድ እችል ዘንድ የመሲሑን የሱስ መንገድ እንዳስተውል አርዳኝ። አሜን።
የወንጌል መልዕክቶችን ቅጂ ለራስዎ ማግኘት ከፈለጉ በዚህ ወረቀት ጀርባ ባለው መረጃ ያግኙን።
Copyright © 2023 by Sharing Hope Publications. ለንግድ ዓላማ አይሁን እንጂ ይህንን ፅሑፍ ማሳተምና ማከፋፈል የተፈቀደ ነው፡፡በዚህ ጽሁፍ ጥቅም ላይ የዋሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተወሰዱት ከ1993፣ 2003 አዲሱ መደበኛ ትርጉም ነው፡፡
የዜና መጽሔታችንን ለማግኘት ይመዝገቡ
አዳዲስ ሕትመቶች ሲወጡ ለማወቅ የመጀመሪያ ይሁኑ
