
በፍርዱ ፈት ያለ ፍርሐት መቆም
ማጠቃለያ
ስለ ፍርድ ቀን ማሰብ በብዙ ሰዎች ልብ ውስጥ ፍርሐት ያነግሣል፡፡ የመጨረሻውን የፍርድ ቀን በአስተማማኝ እንደምናልፍ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? በምድራዊው ችሎት ጠበቃ እኛን ወክሎ ስለ ጉዳያችን እንደሚሟገት ሁሉ፣ እግዚአብሔር—በፍርድ ቀን ስለ እኛ የሚማልድ ጠበቃ እንደሚሰጠን ነግሮናል፡፡ ይህ በራሪ ጽሑፍ እኛን ከዚህ ጠበቃ ጋር በማስተዋወቅ ስለ መጪው ፍርድ ስናስብ እንዴት ዋስትና ማግኘት እንደምንችል ያስተምረናል፡፡
ዓይነት
Tract
አሳታሚ
Sharing Hope Publications
ይገኛል
48 ቋንቋዎች
ገፆች
6
አንድ ቀን ጥዋት አስፈላጊ የሆነ ስብሰባ ላይ ለመገኘት የሆቴል ክፍሌን ለቅቄ ወጣሁ። ዘግይቼ ስለ ነበር ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ ነዳሁ። ጉዞዬን እንዳጋመስኩ ድንገት አንድ የፖሊስ መኮንን አስቆመኝና ወደ ፖሊስ ጣቢያ መሄድ እንዳለብኝ ነገረኝ። ጥፋት እንደ ሠራሁ በሚገባ ስለተገነዘብኩ፣ ብርቱ የመረበሽ እና ረዳተቢስ የመሆን ስሜት ተሰማኝ።
የፖሊስ መኮንኑ የክስ መዝገብ ከከፈተብኝ በኋላ መጥሪያ ለመውሰድ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ፍርድ ቤት ተወሰድኩ። በዚያም ስፍራ አንድ የማውቀውን በጥብቅና ሙያ የተሰማራ ጓደኛዬን አገኘሁት፡፡ ሲያየኝ ገረመው። ፍርድ ቤት ያመጣኝን ጉዳይ ሳብራራለት “አትጨነቅ ጉዳይህን እኔ እይዘዋለሁ” አለኝ። እኔም እጅግ ደስ ተሰኘሁ፡፡ የገዛ ጓደኛዬ ጠበቃዬ ሆኖ ይቆምልኛል!
ይህ ጓደኛዬ በእኔ ፈንታ ጠበቃ ስለሆነልኝ፣ ዳኛው አነስተኛውን የቅጣት እርከን በየኑ፡፡ እግዚአብሔርን እያመሰገንሁ ከፍርድ ቤት ወጣሁ።
በምድራዊ ፈራጅ ፊት መቆም በእርግጥም እጅግ አስፈሪ ቢሆንም፤ በታላቁ የፍርድ ቀን በፈጣሪ ፊት ከመቆም ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር ግን እንደ ምንም ነው። ምናልባት ያ ቀን ነገ ሊሆን ቢችል ተዘጋጅተዋልን?
ለአምላካዊው ፍርድ መዘጋጀት
በቅርቡ ገቢራዊ በሚሆነው የፈጣሪ ፍርድ ዙሪያ የአንዳንድ ሰዎች ምላሽ በግዴለሽነት የተሞላ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ የሚያሰክር መጠጥ ይጠጣሉ፣ ያጨሳሉ፣ ቁማር ይጫወታሉ፣ ወደ ምሽት መዝናኛዎች ይሄዳሉ እንዲሁም አጸያፊ ፊልም ይመለከታሉ። እነዚህ ነገሮች በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጻፉ ሊያውቁ ቢችሉም ነገር ግን በሰይጣን (ወይም ሸይጣን) ማታለያዎች ተይዘዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ጉዳዩ እያሳሰባቸው ያለ አይመስሉም፡፡
ሌሎች ሰዎች ደግሞ ጉዳዩን ከመጠን ባለፈ ፍርሃት ከመመልከታቸው የተነሣ፣ በቀን ውስጥ ወደ ፈጣሪ ከሚያቀርቡት ጸሎት አንዱን እንኳ ለመዝለል አይደፍሩም፡፡ ስለ መቃብር ሥቃይ ወይም ስለ ገሐነም እሳት አብልጠው ከመጨነቃቸው የተነሣ የፈጣሪን ፍቅርና ቸርነት ይረሳሉ፡፡
ሆኖም በፍርድ ቤት እኔ ጠበቃ እንደነበረኝ ሁሉ፣ የአምላክን የፍርድ ሂደትም በሰላም እናልፍ ዘንድ የሚረዳን ጠበቃ ፈጣሪ አቅርቦአል። በፍርዱ ፊት ብቻዎን መቆም የለቦትም!
ለመሆኑ ጠበቃችን ማን ነው?
አንድን ሰው ወክሎ ስለሚቆም ጠበቃ መስማት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ የኃይማኖት ተጉዋዦች በሰሜን አፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በእስያ የተቀደሱ ሥፍራዎችን ይጎበኛሉ። በርካታ ሰዎች አማላጅና ጠበቃ ይሆኑልናል ብለው ባመኗቸው ታላላቅ የኃይማኖት መሪዎች መቃብር ላይ አቀርቅረው ይጸልያሉ፡፡
እነዚያን ታላላቅ መሪዎች ማክበር መልካም ቢሆንም፣ ወደ እነርሱ መጸለይ ወይም ምልጃቸውን መጠየቅ ግን ፈጽሞ ሃራም ነው። ስለሞቱ ለእርስዎ አንዳችም ነገር ማድረግ አይችሉም፡፡ ነቢያት እንኳ ሳይቀር የትንሣኤን ቀን እየተጠባበቁ ያሉት በመቃብር ውስጥ ሆነው ነው፡፡
ሙታን እንዲማልዱልን መጠየቅ ሃራም ቢሆንም፣ የምልጃ ሃሳብ በራሱ ግን ትክክል ነው። ታዲያ የማን ምልጃ ነው በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት ያለው?
ሕያው የሆነ እርሱ መሆን አለበት (ምክንያቱም ሙታን እኛን ወክለው መናገር አይችሉምና)።
ኃጢአት የሌለበት መሆን አለበት (ምክንያቱም በሕግ የተፈረደበት ለሌሎች ጠበቃ ሆኖ መቆም አይችልም)።
እነዚህን መስፈርቶች ሊያሟላ የሚችለው ማን ነው? ኢሳ አል-መሲህ ተብሎ ከሚጠራው በሰማይ ሕያው ሆኖ ከሚኖረውና ፍጹም ንጹህ ከሆነው ከውዱ የሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ማንም የለም።
አስቡበት—ኃጢአት ዐልባ ነኝ ለማለት የሚችል ሌላ አለ? አዳም የተከለከለውን ፍሬ በላ፣ ኖህ (ኑህ) በወይን ጠጅ ሰከረ፣ አብራሃም (ኢብራሂም) ዋሸ፣ ሙሴ (ሙሳ) ሰው ገደለ፣ ዳዊት (ዳውድ) የሌላ ሰውን ሚስት ሰረቀ። አንዲት ጥፋት ፈጽሞ ያላጠፋ ወይም ይቅርታ መጠየቅ ፈጽሞ ያላስፈለገው አንድም እንኳ ነቢይ አታገኙም።
የሱስ ክርስቶስ ግን ፈጽሞ ምንም ኃጢአት አልሠራም። እራሱ ተናግሮአል፣ “የላከኝ እርሱ ከኔ ጋር አለ...እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና” (ኢንጂል በመባልም ከሚታወቁት ከወንጌላቱ፣ ዮሐንስ 8:29)።
ፍርድን በሙሉ ሰላም መጋፈጥ
የሱስ ክርስቶስ በሰማይ ሕያው ሆኖ ያለና ኃጢአት የሌለበት ነው። እርሱ ለእኔና ለእርስዎ ጠበቃ ሆኖ ይቆምልን ዘንድ ዝግጁ ነው፡፡ ደግሞም በቅርቡ ዳግመኛ ይገለጣል፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ ተመልሶ የሚመጣ ከሆነ፣ ይህ ማለት፣ የሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው ነቢይ ነው ማለት ነው። አዎ፣ ከነቢይም የሚበልጥ—ጠበቃችን፣ ጌታችን፣ በፍርድ ቀንም ሰላማችን ነው። እንዲህ ሲል ነግሮናል፣ “እውነት እውነት እላችኋለሁ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አያይም” (የዮሐንስ ወንጌል: 8:51)።
የሱስ ሞቶ አልቀረም፤ ነገር ግን ሕያው ነው! ደግሞም የራሱን ሕዝቦች እነሆ ዛሬም በምድር ላይ እየገነባ ይገኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ነጭ የለበሰ ሰው ሆኖ በህልም በመታየት ወይም በስሙ ወደ ፈጣሪ ስንጸልይ ተአምር በማድረግ ሰዎችን ወደ እርሱ የተለዩ ሕዝቦች ይጋብዛል።
በፍርድ ቀን ሰላም ይኖርዎ ዘንድ ፍላጎትዎ ነውን? በየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን እምነት መስክሩ። ዛሬ በመቃብር ውስጥ በሚገኙ እና በፈጣሪ የፍርድ ቀን ዕጣ ፈንታቸው በማይታወቅ ፍጡራን ላይ እምነታችንን ለምን እንጥላለን? የየሱስ በሰማይ መኖር የተረጋገጠ ሐቅ ነው፡፡ ልክ በችሎት ውስጥ እንደነበረው ጠበቃ ጓደኛዬ ሁሉ፣ እነሆ እርሱ ይረዳናል።
ምናልባትም እንዲህ ያለውን ድንቅ ነገር ሲሰሙ እውነት ይሆን? ብለው ያስቡ ይሆናል፡፡ የሱስ እንዲህ ብሎአል፣ “ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ” (የዮሐንስ ወንጌል: 14:14)። እየነገርኳችሁ ያለው ነገር እውነት እንደሆነ ለማወቅ፣ ፈትኑ። የሱስ ለሕይወት አጣዳፊ ጉዳዮች አሁን መፍትሔ የሚሆን ኃይል ያለው ከሆነ፣ ጠበቃችን ሆኖ ይቆም ዘንድ በእርግጥም የታመነ ነው፡፡ ወደ ፈጣሪ በእውነተኛ ልብ በየሱስ ስም ጸልዩና የሚሆነውን ተመልከቱ። እንዲህ ብለው መጸለይ ይችላሉ፡-
ጌታ ሆይ፣ በፍርድ ቀን ጠበቃችን ይሆን ዘንድ የሾምከው በእርግጥ የሱስ እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ። አቤቱ ይህ እውነት ከሆነ እባክህ (እዚህ ላይ የሚፈልጉትን ያስገቡ) ጸሎቴን መልስልኝ። ይህንንም በየሱስ ክርስቶስ ስም እጠይቃለሁ። አሜን።
የሱስ ክርስቶስን እንዴት መከተል እንደሚችሉ በተጨማሪ ማወቅ ከፈለጉ በወረቀቱ ጀርባ ላይ ባለው መረጃ ይጻፉልን።
Copyright © 2023 by Sharing Hope Publications. ለንግድ ዓላማ አይሁን እንጂ ይህንን ፅሑፍ ማሳተምና ማከፋፈል የተፈቀደ ነው፡፡በዚህ ጽሁፍ ጥቅም ላይ የዋሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተወሰዱት ከ1993፣ 2003 አዲሱ መደበኛ ትርጉም ነው፡፡
የዜና መጽሔታችንን ለማግኘት ይመዝገቡ
አዳዲስ ሕትመቶች ሲወጡ ለማወቅ የመጀመሪያ ይሁኑ
