የስደት ግብዣ!

የስደት ግብዣ!

ማጠቃለያ

የተሻለ መኖሪያ ስፍራ ይናፍቁ ይሆን? አስተማማኝ ደኅንነት፣ ደስታ እና ዕረፍት የሰፈነበት ቦታ? እያንዳንዳችን በገነት እንኖር ዘንድ ስለተፈጠርን ይህ ዓለም ሊሰጠን የማይችለውን አንዳች ነገር እንናፍቃለን፡፡ መሲሁ የሱስ ወደዚያ ስፍራ ሄዷል፡፡ እርሱ መንገዱን ያውቃል፤ እንዲያውም ራሱን “መንገዱ” እኔ ነኝ በማለት ይጠራል፡፡ ይህ በራሪ ጽሑፍ በገነት ዜግነት ለማግኘት እንድንዘጋጅ ስለሚረዳን ስለ የሱስ ጠቃሚ እውነቶችን ይገልጻል፡፡

አውርድ

አብዱል ማሌክ እርጅና የተጫናቸው አረጋዊ ነበሩ፡፡ ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ካጡ በኋላ ከአይሲስ ጥቃት ለማምለጥ ኢራቅን ጥለው ወጡ፡፡ በወቅቱ ብቻቸውን በዮርዳኖስ ስደተኛ ሆነው ቢኖሩም፤ ጥቂት የተስፋ ጭላንጭል ግን ነበር ፡፡

በካናዳ የመኖር እና የመሥራት ዕድል ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል ሊያመቻችላቸው እንደሚሞክር አንድ በዚያው የሚኖር የአጎታቸው ልጅ አበሰራቸው፡፡ ጉዳዩ ክፉኛ ቀልባቸውን የሳበው አብዱል ሜሌክ ቪዛ ለማግኘት የሚያስችላቸውን ሂደት በመጀመር በዚያ እኖራለሁ ብለው የተመኙትን ቀለል ያለ ሕይወት ከወዲሁ አለሙ፡፡ በመጨረሻም፣ ከበርካታ ዓመታት ጥበቃ በኋላ፣ ወደ ካናዳ እንዲገቡ ተፈቀደላቸው፡፡ አብዱል-ማሌክ በደስታ ፋነደቁ!

ሆኖም ደስታቸው አጭር ነበር፡፡ ካናዳ እንደ ደረሱ ሕይወት ከስደት በኋላ ቀላል አለመሆኑን ተረዱ፡፡ የሚሠሩት ሥራ ቀኑን ሙሉ እንደቆሙ ያውላቸዋል፡፡ በዚያ ላይ ጎረቤቶቻቸው ዝግ ብለው መናገር አይችሉም–ይጯጯኻሉ፡፡ የሕዝብ ማመላለሻን ትራንስፖርትም ሆነ የእንግሊዝኛን ቋንቋ ባህሪ ለረዳት ለእርሳቸው ቀላል አልሆነም!

አብዱል ሜሌክ ወደ ተሻለ ስፍራ መሄድ የሁልጊዜ ሕልማቸው የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን እዚያ ከደረሱም በኋላ ልባቸው እንደተሠበረ መቀጠሉን አስተዋሉ፡፡ ውስጣቸው ባገኘው ብሎ የሚናፍቀው ስፍራ በዚህ ምድር ይገኝ ይሆን–ወይስ እስከ ገነት ድረስ መጠበቅ ይኖርባቸዋል? አብዱል ማሌክ ማሰላሰል ጀመሩ፡፡

ስደት ወደ ገነት፤

አብዱል ማሌክ የተሰማቸው ዓይነት ስሜት እርስዎንም ተሰምቶት ይሆን? ይህ በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ሥር የሰደደውና ለተሻለ መኖሪያ ያለው ጥማት የሚረካው እውነተኛ ቤታችን ወደሆነችው ወደ ገነት መግባት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቅርቡ ፍጻሜ የሚያገኝ ምኞት ነው፡፡ የመምጫ ሰዓቱ ምልክቶች ዓይኖቻችን እያዩ ፍጻሜ እያገኙና ይህ ምድር በፍጥነት ወደ ፍጻሜ እየመጣ ነው፡፡

የአይሁድ፣ የክርስቲያን እና የሙስሊም ኃይማኖታዊ መጻሕፍት ሁሉም የመጨረሻውን ምዕራፍ ማለትም ከዚህ ዓለም ወደ ተሻለውና ቀጣዩ “የምንሰደድበትን” የምጽአትን ጊዜ ለበርካታ መቶ ዓመታት ሲተነብዩ ኖረዋል፡፡ ሦስቱም ቤተ እምነቶች የእነዚህ የመጨረሻ ክስተቶች መደምደሚየ መሲሕ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡   

የሚገርመው ነገር፣ ይህ በክርስትና እና በእስልምና ውስጥ ያለው መሲሕ ከየሱስ ክርስቶስ (ኢሳ አል ማሲህ በመባልም ይታወቃል) ሌላ ማንም አይደለም፡፡ እርሱ በፍልስጥኤም ይኖር በነበረበት ወቅት መሲህ የነበረ ቢሆንም፣ ካለፉት 2,000 ዓመታት አንስቶ ግን በገነት እየኖረ ይገኛል፡፡ ውሎ አድሮ፣ እነሆ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ይመለሳል፡፡

የየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት በከበረ መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን፤ ሙስሊሞችም ዳግመኛ ይመለሳል ብለው ያምናሉ፡፡ “እርሱም (ዒሳ) ለሰዓቲቱ (ማወቂያ) በእርግጥ ምልክት ነው፡፡ ‘በእርሷም አትጠራጠሩ፡፡ ተከተሉኝም፤ ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው’ (በላቸው) (አዝ-ዙክሩፍ 43:61)፡፡”

አንድ የስደተኞች ጉዳይ ባልደረባ መኮንን ቪዛ እንዴት እንደሚገኝ ጠቃሚ ምሪት እንደሚሰጥ ሁሉ፣ ወደ ገነት የሚወስደውን ቀጥተኛ መንገድ እናውቅ ዘንድ ለእርሱ ምልክት ትኩረት እንድንሰጥ የሱስ ክርስቶስ ይጋብዘናል፡፡

የሱስ ገነት ምን ትመስላለች ሲል ተናገረ?

ኢንጂል በመባል በሚታወቁት የወንጌል መልእክቶች የሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ተናግሮአል፡ “የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው፡፡ ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ፡፡” (የዮሐንስ ወንጌል፡ 14:2, 3)፡፡ የሱስ ክርስቶስ ወደ ገነት ሊወስደን እንደሚችል ይናገራል፡፡

ስለዚያ ስፍራም ግሩም የሆኑ መልእክቶችን እንዲህ ሲል፣ በጨረፍታ ሰጥቶአል፡፡

  • “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም” (ራእይ፡ 21፡4)፡፡

  •  ውብ መኖሪያ ቤት ይኖረናል፤ (ዮሐንስ፡ 14፡2)፡፡

  •  ሴቶች እና ወንዶች እኩል ክብርና መብት ይኖራቸዋል፤ (ገላትያ፡ 3፡28)፡፡

  • በብርሃን፣ በጽድቅና በደስታ የተሞላ ነው፤ (ራእይ፡ 21:21-25)፡፡

ልባችን በእውነት የሚናፍቀው ይህንኑ ስፍራ ነው! 

የሱስ ክርስቶስ ለሁለተኛ ጊዜ ለምን ይመጣል?

ነገር ግን ፈጣሪ ብዙ ነቢያትንና ቅዱሳን መልዕክተኞችን ልኳል፡፡ የሱስ ክርስቶስ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲመጣ ለምን ተመረጠ? ይህን ጥያቄ ከተመሳሳዩ የስደት ጉዳይ ምሳሌ ጋር አያይዞ መመለስ ቀላል ነው፡፡ ቪዛ ማግኘት ቀላል ስላልሆነ ብዙ ሰዎች አካሄዱን የሚያውቅ የስደተኞች የሕግ ባለሙያ (ጠበቃ) ይቀጥራሉ፡፡ የሚመራን ካለ ይረዳን ዘንድ ልንተማመንበት እንችላለን፡፡

በተመሳሳይ፣ ለሁለተኛ ጊዜ የሚገለጠው የሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፣ እርሱ ወደ ገነት የሚወስደውን መንገድ ስለሚያውቀው ወደዚያ ይመራን ዘንድ ይችላል፡፡ “መንገዱ እኔ ነኝ፣ እውነት እና ሕይወትም እኔው ነኝ” (ዮሐንስ፡ 14፡6) በማለት እርሱ ራሱ ተናግሮአል፡፡

በፈጣሪ የተላከ እያንዳንዱ ነቢይና መልእክተኛ ሥህተት ሠርቶአል፣ ይቅርታ መጠየቅም አስፈልጎታል፡፡ የሱስ ክርስቶስ ግን አላስፈለገውም፡፡ በምድር በኖረበት 33 ዓመታት ውስጥ ኃጢአት አልተገኘበትም፡፡ በዚህ የተነሣ ወዲያውኑ ወደ ገነት ተወሰደ፡፡

ወደ ገነት ለመግባት የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች እንዴት ማሟላት እንዳለብን ለማወቅ ኃጢአት ዐልባ ከሆነው ከየሱስ ክርስቶስ መማር አለብን፡፡ ወደ ገነት መግባት እንደምንችል እርግጠኞች መሆን የምንችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ምስጋና ይግባውና የእርሱ መጽሐፍ ከሆነው፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ መማር እንችላለን፡፡ 

ለየሱስ ክርስቶስ መመለስ መዘጋጀት፤

ወደ ተሻለ ሥፍራ ስለመጓዝዎ እርግጠኛ መሆን በመቻልዎ ደስታ ተሰማዎት? በገነት ባለው በክብር የተሞላ የፈጣሪ መንግሥት ዜጋ ይሆኑ ዘንድ ተጋብዘዋል! የሱስ ክርስቶስ ወደዚያ ውብ ሥፍራ ሊውስደን በቅርቡ ይመጣል፡፡

በዚያ የፍርድ ቀን ራሳቸው ምን እንደሚገጥማቸው የማያውቁ ሰብአዊ ፍጡራንን እየተከተላችሁ ይሆን?  ከየሱስ ክርስቶስ ጋር እስከሆኑ ድረስ መጠራጠር የለቦትም፡፡ የሱስ ክርስቶስ ቀጥተኛውን መንገድ ይመራዎ ዘንድ ፈጣሪን ይጠይቁ፡፡ የሚከተለው ዓይነት ልመና ማቅረብ ይችላሉ፡-

ጌታ ሆይ፣ ልቤ የተሻለውን ሥፍራ ይናፍቃል፡፡ እባክህን እኔን እና የምወዳቸውን ወገኖች ከዚህ ዓለም ችግሮች ነጻ አውጣን፡፡ ጊዜው አጭር እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ለእኔ ወዳዘጋጀኸው ግሩም ሥፍራ መግባት እችል ዘንድ እባክህ ምሪት ስጠኝ፡፡ አሜን፡፡

የወንጌልን የታመነ ቅጂ ማግኘት ከፈለጉ በዚህ ወረቀት ጀርባ ባለው አድራሻ ያግኙን፡፡

የአማርኛውን ቁርአን የተረጎሙት መሀመድ ሳዲቅ እና መሀመድ ሳኒ ሀቢብ ናቸው፡፡Copyright © 2023 by Sharing Hope Publications. ለንግድ ዓላማ አይሁን እንጂ ይህንን ፅሑፍ ማሳተምና ማከፋፈል የተፈቀደ ነው፡፡
በዚህ ጽሁፍ ጥቅም ላይ የዋሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተወሰዱት ከ1993፣ 2003 አዲሱ መደበኛ ትርጉም ነው፡፡

የዜና መጽሔታችንን ለማግኘት ይመዝገቡ

አዳዲስ ሕትመቶች ሲወጡ ለማወቅ የመጀመሪያ ይሁኑ

newsletter-cover